በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ወጥ የሆነ አሰራር በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለፁ።

የክልሉ የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት ያጠናውን የኢንቨስትመንት ሪፎርም ጥናት ሰነድን ለካቢኔ አቅርቧል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለካቢኔ በቀረበዉ የኢንቨስትመንት ሪፎርም ጥናት ሰነድ ላይ እንዳሉት ክልሉን ከኢንቨስትመንት ዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌሎች ክልሎች የአሰራር ልምድ መውሰዱ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
በክልሉ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን እና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የባለሀብቶች ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማሚያግዝ ወጥ አሰራርን በመዘርጋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመን ዘርፎች ለመሰማራት የሚመጡ ባለሀብቶችን የመስራት አቅማቸውን ለይቶ ማሰራት ትኩረት የሚደረግበት ጉዳይ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው ክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት ተጠቅመው የተለያዩ ባለብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ ባለሀብቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ የክልሉን ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አሳውቀዋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ተቋምም አሰራሩን በማጠናከር እና በማዘመን ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የክትትል እና ድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጣላሉ ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ አሰራር ለማሻሻል የሚያስችል ከሌሎች የክልል ተቋማት የኢንቨስትመንት ሪፎርም ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።
ይህም በክልሉ በሚሰራው የኢንቨስትመንት ስራ ክልሉን እና ማህበረሰቡን የሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የኢንቨስትመንት አሰራሩን ለማሻሻል እና ውጤቶችን ለማስመዝገብ የተደረገዉ ጥናት ተገቢ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሌሎች የካቢኔ አባላት ናቸው፡፡
የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ ባለሀብቶችን ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ዉሳኔ በመስጠት ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ማድረግ እንደሚባውም አስገንዝበዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችም የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅምን መፍጠር የሚጠበቅባቸው መሆኑን አንስተዋል።
በኢንቨስትመንት ፍቃድ አሰጣጥ እና በሌሎች የሚስተዋሉ አለመናበብ ችግሮችን በመቅረፍ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን በመተግበር በቀጣይ አመርቂ ዉጤቶችን ለማስመዝገብ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ሀሳባቸውን አንስተዋል።
 
 
 
 


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *