(አሶሳ፣ ሚያዚያ 23/2017 ዓ/ም) በክልሉ ማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር ገለጹ።በአቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር የተመራ ልዑክ በማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።
የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀረጹ የተለያዩ ኤኒሼትቮችን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር ተናግረዋል። በልዩ ወረዳው በአሁኑ ወቅት ሠላማዊ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመው፣ የተገኘው ሰላም በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በልዩ ወረዳው እየተተገበሩ የሚገኙ የመስኖ ልማት፣ የዶሮ መንደር፣ የማር መንደር፣ የእንቁላል መንደር እና ሌሎች የልማት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በክልሉ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ አየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አቶ ኢሳቅ ተናግረዋል።
የማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ከማል እድሪስ፣ አርሶ አደሩ ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ የመስኖ ልማት ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በልዩ ወረዳው ከ15ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የመስኖ ልማት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ከወተትና ሌሎች የሌማት ትሩፋት ስራዎች ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።የልዩ ወረዳው ግብርና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በሽር ፍድሌላ፣ ከ6 ሺ 400 በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑኑን ጠቅሰዋል። ከመስኖ ልማት ሥራው 463 ሺህ 440 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ያሉት ኃላፊው፣ እስካሁን ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።


