(አሶሳ፣ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ከህግ ማስከበር ጎን ለጎን ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በ2017 በጀት ዓመት በገበያ ማረጋጋትና እና የኑሮ ዉድነት ቅነሳ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በተረጂነት ቅነሳ የተከናወኑ ሥራዎችን ገምግመዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስር ኢብራሂም፤ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደረገ ክትትል የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ምርት በመደበቅ የኑሮ ውድነትቱን አባብሰው በተገኙ 6 ሺህ 163 የንግድ ተቋማት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል መወሰዱን ገልጸዋል።
በንግድ ተቋማቱ ላይ ከማሸግ ጀምሮ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርሱ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ አብዱልአዚዝ፤ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን የተረጂነት ቅነሳን በሁሉም ወረዳዎች ለመግበር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ በምርት ዘመኑ 2 ሺህ 607 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ርብርብ አየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በተከናወነ የአካባቢ ጸጋን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ሥራ ፈጠራ ሥራ በግብርና፣ አገልግሎትና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለ28 ሺህ 610 ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል ተፈጥሯል የፈጠረ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ 89 በመቶ መሆኑንም ተገልጿል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ እና ሕብረተሰቡን የሚያማርሩ ነጋዴዎች ላይ የተጀመረውን የህግ ማስከበር ሥራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ምርታማነትን ማሳደግ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አቶ ጌታሁን፣ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት የሆኑ ሰው ሰራሽ ችግሮችን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በ2016/17 የምርት ዘመን የተጀመረውን አበረታች ጥረት በተያዘው የምርት በሁሉም ወረዳዎች ማስቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር፣ ምርታማነትን ከመጨመር ጎን ለጎን በንግድ ስርዓቱ ላይ ጠንካራ የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል።


